ዛሬም እየተገደልን ነው… ሲደብር! (አቤ ቶኪቻው)

ሰሞኑን ከተሰሙ አስደንጋጭ ዜናዎች ውስጥ የሚከተለው ይገኛል…

“በዛሬዉ እለት በአርሲ አሳሳ ከተማ የጁምአ ሰላት ከተሰገደ በኋላ ሼህ ሱዑድ በአንድ መስጂድ ዳዕዎ አድርገዉ ሲወጡ በፓሊስ በመያዛቸዉ፤ የአካባቢዉ ሙስሊም ህብረተሰብ “ሼሁ ለምን ይታሰራሉ ምንም ጥፋት አልፈፀሙም” በሚል ለማስለቀቅ ሲሞክሩ ከፓሊሶች ጋር በተፈጠረዉ አለመግባባት ፓሊስ በከፈተዉ ተኩስ እስካሁን ባለዉ መረጃ መሠረት አምስት(5) ሰዎች መገደላቸዉና ብዙ ሰዎች መቁሰላቸዉን የአካባቢዉ ምንጮች ገለፁ:: ከተገደሉት ሰዎች መካከል ሼህ ኸድር የሚባሉ ታላቅ አሊም እንደሚገኙበትም ምንጮች ጨምረዉ ገልፀዎል:: እንደሚታወሰዉ ሼህ ሱዑድ ሻሸመኔ በተካሄደዉ ስብሰባ ላይ “ኢህአዴግን ለሀያ አመታት ስንደግፈዉ ኖረን አሁን እንዴት አሸባሪ አክራሪ ብሎ ይወነጅለናል” በማለት የተሰማቸዉን ቅሬታ በስብሰባዉ ላይ ገልፀዉ እንደነበር የሚታወስ ነዉ::

ይህንን ያገኘሁት ከአንድ የፌስ ቡክ ወዳጃችን ግድግዳ ላይ ነው። ዜናውን ሚዛናዊ ለማድረግ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ደግሞ ቀጥሎ እጠቅሳለሁ።

“በአርሲ ዞን አሳሳ ከተማ በሙስሊም አክራሪነት ሰዎችን ሲያደራጅ እና በመንግስት እና በህዝብ ላይ ጀሀድ ሲያውጅ የነበረ የነበረ አንድ ግለሰብ በቁጥጠር ስር ዋለ። ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋለው በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሆኑን ኢኒስፔክተር (ስማቸው ጠፍቶብኛል) ብቻ አንድ የፖሊስ አባል ኃላፊ ተናግረዋል። ሰውየው አያይዘው እንደተናገሩት በወቅቱ ግለሰቡ ያደራጃቸው አንዳንድ አክራሪዎች እና የተለየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ግብረ አበሮቹ ባነሱት ግርግር የአሳሳ ከተማ ፖሊስ ጣብያ ወድሞ አራት ሰዎች ሲሞቱ አስር ፖሊሶች ቆስለዋል።”

ቀጥሎ የኔ አስተያየት ይከተላል።

እንግዲህ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ስንሰማ ትርጉም አዋቂ እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው። “በመንግስት እና በህዝብ ላይ ጀሀድ ሲያውጅ የነበረ አንድ ግለሰብ” ማለት ምን ማለት ነው? ያልን እንደሆነ መዝገበ ቃላታችን “የመንግስትን በሀይማኖት ጣልቃ ገብነት የተቃወመ” በሚል ይፈታልናል።

ያው እንደሚተወቀው ሙስሊም ወንድሞቻችን፤ “መንግስት የራሱን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሃይማኖት ይንከባከብ የኛን ሃይማኖት ለኛው ይተውልን!” ብለው ድምፃቸውን ማሰማት ከጀመሩ ቆይተዋል። ኢቲቪ እና መንግስት ብዙ ሀሳብ ስላለባቸው ይህንን ዜና ስንከታተል እንደቆየን ረስተውታል መሰል፤ “በመንግስት እና በህዝብ ላይ ጀሀድ ሲያውጅ የነበረ ግለሰብ” ይለናል። ለመሆኑ ይህ ትርጉም ይሰጣልን!? መንግስትንም ህዝብንም ላጥፋ የሚል ጀሀድ ታይቶ ይታወቃልን?  እኒህ ማንንም ያልገደሉ የሀይማኖት አባት ጀሀድ አወጁ ከተባሉስ በከተማው  አምስት ሰዎችን የገደለው መንግስት ምን አወጀ ሊባል ነው…?

ወዳጄ ባለፈው ግዜ ያስታውሱ እንደሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማቸው ቀርበው በአርሲ የአልቃኢዳ ሴል ተገኝቷል! ብለው ያለምንም “ሼ” ሲናገሩ ይህንን መጠርጠር ተገቢ ነበር። የምር ግን፤ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አምርረውብናል። አንዳንዶች እንደሚሏቸው ከሆነ፤ “እኒህ ሰውዬ መጀመሪያ ኑሯችንን ዘቀዘቁ ዝም አልን፤ በመቀጠል ባንዲራችንን ዘቀዘቁ አሁንም ተሳስተው ይሆናል ብለን ዝም አልን፤ ቀጥሎ ደግሞ እያንዳንዳችንን ሊዘቀዝቁን ቆርጠው ተነስተዋል!” ይሏቸዋል። እኔ እንኳ እስከዛ መድረሳቸውን እጠራጠራለሁ። ነገር ግን በእውነቱ ጥምድ አድርገው የያዙን ይመስለኛል። ምን እንዳስቀየምናቸው እንጃ… እንዴ አስቡት እስቲ “አልቃይዳ” ከማለት ውጪ ምን ሊሉን ይችላሉ። በዚህ አይነት እኮ ሰውዬው የአሜሪካ ጦር ራሱ አካባቢውን ገብቶ እንዲደበድብ ሊጠይቁ ይቻላሉ ማለት ነው…!

የሆነ ሆኖ ዛሬም ተቃውሞ እና አመፅ ስለተነሳ ሰዎች ይገደላሉ… ሲደብር። አረ መንግስታችን በናትህ የጉርምስና መንፈስህን ገስፀው!

Advertisements

ለሰንበት፤ የበኃይሌ ቢን ላደን

ዛሬ ሰንበት ነው። እንዴት አደራችሁ!  ነገ ጠዋት በሰፊው እስክንገናኝ  ለሰንበት ታኽል ግን የሆነች ነገር መሰንዘር ግድ ይላል ብዬ አሰብኩ። አስቤስ …? ትላንት የበሀይሉ ገ/ኢግዚአብሔር አዲስ መፅሐፍ “ኑሮ እና ፖለቲካ” እጄ ገባ። እንዴት እንዴት አይነት ጨዋታዎችን ይዟል መሰለችሁ!? በእውነቱ  ዛሬ በማውጊያችን አንድ ለሰንበት ጣል ባደርግ ደስ እንደሚላችሁ ርግጠኛ ሆንኩ… ሆኜም እነሆ አልኩ፤

የቢል ነገር

እንደ ትናንት ምሳ የተመገብንበት ቤት እንደ ዛሬ ሁደን ምሳ አዘዝን ይህቺ ምግብ ቤት ከሌሎች ምግብ ቤቶች አንፃር ዋጋዋ ደህና ናት ተብሎ በኛ ዘንድ ሞገስ ያገኘች ቤት ነበረች።

ከአቅም አንፃር ደግሞ በጣም ደህና እንዲሆንልን አምስት ስድስት ሆነን በማኅበር አዝዘን እንመገብ ነበር። ምግቡ መጣ፤ ከጥሩ የምሳ ጨዋታ ጋር ተበላ፤ በጥርስ እንጨት ጥርሳችንን እየጎረጎርን ሂሳብ እንዲቀበለን አስተናጋጃችንን ጠራን። እስኪመጣም ዐይናችንን ወደ ተከፈተው ቴሌቪዥን ሰደድን።

“የቢን ላደን ሞት አነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ነው!” ይላል ዘገባው። ለበላነው ምግብ ማወራረጃ ይሆን ዘንድ የኛም የውይይት ርዕስ ቢን ላደን ሆነ።፡

“ለመሆኑ ቢን ላደን የሚባል ሰው በህይወት ነበረ?”

“እንዴ ምን ነካህ አለ እንጂ!”

“እውነት ግን ለምን ሬሳውን አያሳዩንም?”

“ያልነበረ ሰው መቼም ሞተ ተብሎ አይነገርም!”

“ቢን ላደን ለኦባማ ስልጣን ማራዘሚያ ጠቀመው!”

አስተናጋጁ ከቆይታ በኋላ እንደ መፅሐፍ ተገላጭ የሂሳብ መቀበያ ውስጥ ቢል ሸጉጦ ሰጠን፤ ቢሉ ቢነበብ ትላንት በበላነው በእያንዳንዱ ምግብ ላይ በትንሹ ስድስት ብር ተጨምሯል።፡

“ምንድነው ይሄ?” ቢሉን እያየ ያለ ወዳጃችን ፊቱን አኮሳትሮ ጠየቀ። በእንዲህ አይነት ጥያቄ የተሰላቸው አስተናጋጅ ፊቱን አዙሮ የዋጋ ዝርዝር የተፃፈበትን ነጭ ሰሌዳ አሳየን። የዋጋ ጭማሪው እውነት ነው። 34 ብር የነበረው የበግ ጥብስ 40 ብር ብሎ ይጀምራል ዝርዝሩ።

“ለምንድነው በአንድ ቀን ይሄ ሁሉ ጭማሪ!?”

“ቢል መቁረጥ ዛሬ ስለጀመርን!” በታከተ ድምፅ አስተናጋጁ መለሰ።

“ቢል ከምትሉ ቢላ ብትሉ አይሻልም!?” በምሬት ሌላው ወዳጃችን።

ሻዩ፣ ማኪያቶው፣ ሽሮው፣ ቀይ ወጡ… /ሆድ ስለባሰኝ በዚሁ ልቀጥልበት፤- ትራንስፖርቱ፣ ስኳሩ፣ ወይ ዘይት፤ ዘይት የቅቤ ረዳት ተዋናይ ተደርጎ መጠራት ከጀመረ ጀምሮ ዋጋው የማይቀመስ ብቻ ሳይሆን በፈለጉት ዋጋ ታስሶ የማይገኝ ሆኗል። “ሸኖ ቅቤ፤ ሸኖ ለጋ፤ ሻዲ ለጋ…” ያኔ ሲሉት መጠርጠር ነበረብን። … ነዳጁ፣ ሰዉ፣ ስጋው፣ ግብረ ስጋው… አዬዬ ምን ይሻላል?/ ሁሉ ነገር በየቀኑ ይጨምራል። “የዚህ የኑሮ ውድነት ጦስ መጨረሻው ምን ይሆን?” ስጋት ባጀበው ዝግ ባለ ድምፅ ራሴን ጠየቅኩ።

“ወይ ጉድ” አለ አንዱ ወዳጃችን በመሃል አንዳች የታወሰው ነገር ያለ በሚመስል።

“ምን ሆንክ?”

“ቢል ላደን መቼ ሞተ?”

“እንዴት?”

“በህይወት አለ እኮ፤ ያውም እዚችው እኛው ምድር!”

“ምን ማለት ነው?”

“ቢል ላደን መጥቶ ይኸው እኛን እየጨረሰን እኮ ነው።” አለ ንግግሩን ይበልጥ እያሻሻለ። የጓደኛችን ንግግር ሁላችንም የገባን ዘግይቶ ነው።፡ነገሩ ቅኔ መሆኑ ነው፤ ቢል ላደን። እውነትም ቢል ለአደን።

“እንገዛ ነበር እቃ በጥሩ ዋጋ፤

ቢል ላደን መጣና ኑሯችን ተናጋ።” ብንለውስ?

በሀይሌን እናመሰግናለን ብዕርህ ትባረክ ብለንም እንመርቃለን። መልካም ሰንበት ይሁንልዎ ወዳጄ!

ፕሮፌሰር መስፍን 82 ዓመታቸው ተከበረ

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምን ሚያዝያ 16 ቀን 2004 ዓ.ም የልደት በዓላቸው ነበር። ይህንኑ አስመልክቶ ዛሬ በርካታ ወጣቶች ቤታቸው ድረስ ሄደው ልደታቸውን አክብረውላቸዋል። (በቅንፍም ታድያ ባዶ እጃቸውን አይደለም የተለያዩ ስጦታዎችን ይዘውላቸው እንጂ! ብዬ እጨምራለሁ።)  በፕሮግራሙ ላይ ከተገኙት እና ለፕሮፌሰር መስፍን የአክብሮት ስጦታ ካበረከቱ ወጣቶች መካከል ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አንዱ ነበር!

እኔም ብኖር ኖሮ አልቀርም።  እናም አምልጦኛል። ቢሆንም ግን በዝች መልዕክት ማስተላለፊያ ፕሮፍ እንኳን አደረስዎ በቀጣይም ረጅም እድሜን እመኝልዎታለሁ! ለማለት እወዳለሁ።፡

ቀጥሎ ከጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ “ፒያሳ” መፅሐፍ ውስጥ የሚከተለውን እንድናነብ እጋብዛለሁ፤ ትንሽ ለመንደርደር ከየት እንጀምር…. አዎ…

“… በ1950 የስዊዲኑ ኖርቺፒንግ ቡድን ለሶስት ግጥሚያዎች መጥቶ ሲጫወት ያሁኑ ስታድየም ገና በመሰራት ላይ መሆኑን አስታውሳለሁ። በባዶ እግራቸው ይጫወቱ የነበሩት ጫማ በልካቸው ፒያሳ እያሰፉ መጫወት ጀመሩ።

የኛ ጫማ ሰፊዎች የፈረንጁን ሞዴል እያዩ የሚሰሩ ቀልጣፎች መሆናቸው ተመስክሮላቸዋል። ለመለካትም ሆነ ፕሮቫ ለማድረግ የሚሄደውን ቡና ወይም ሻይ መጋበዝ ተለምዷል። የብስክሌት ተወዳዳሪ የነበረው አቶ አበበ ማሞ ጥሩ ጫማ ሰፊ ነበር። የአስመራና የድሬደዋ ቡድኖች በኢትዮጵያ ሻምፒዮና መካፈል በመጀመራቸው የፉትቦል ጨዋታው ተስፋፋ። ከጥንት ጀምሮ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብዙ ቀልጣፋ ተጫዋቾች ስለነበራቸው ለልዩ ልዩ ክለቦች ይጫወታሉ።

በዚያን ግዜ በነ ጌታቸው መድህኔ፣ መስፍን ወልደማርያም፣ ኃይሉ አፈወርቅ፣ ልዑል ሰገድ በቀለ፣ ንጉሴ ፍትአወቅ፣ እልፍአግድ ጎበና፣ ፀጋዬ በቀለ፣ ዘውዴ ሳሙኤል እና ሌሎችም የነበሩበት የተፈሪ መኮንን ት/ቤት ቡድን የጦር ሰራዊትን ቡድን አሸንፏል። ወዳጄ ፕሮፌሰር መስፍን ወለወደማርያም በተከላካይ ስፍራ ይጫወት ስለነበር አሁንም የመከላከል ተግባሩን ቀጥሏል። ምንም አንኳ አርቢተሩ ቀይ ካርድ እያሳየ ቃሊቲ ቢከተውም፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ፖለቲካ ቡድን መጫወቱን አላቋረጠም።”

ጋሽ ፍቅሩን እያመሰገንን ፕሮፌሰር መስፍን በቀጣይም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ፖለቲካ ቡድን በተከላካይ ስፍራ እየተጫወቱ እንከኖቻችንን ይከላከሉልን ዘንድ በድጋሚ ረዥም ዕድሜ ይስጥልን ብለን እንመርቃለን!

በመጨረሻም

“አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ” የተሰኘው የፕሮፌሰር መስፍን መፅሀፍ ደርሶኛል። ላኪዎቼም አድራሾቼም እግዜር ይስጥልኝ አሁን ቶሎ ብዬ እርሱን ማንበብ አለብኝ!

ከጋሽ ስብሐት ጨዋታዎች… አንድ

አንጋፋው ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር ነብሱን ይማረው እያልን ማውራት ከጀመርን ሰማንያ ቀን በቅርቡ እንደሚሞላው አንድ ወዳጃችን በለጠፈው ማስታወሻ አስታውሶናል። እንደውም ዛሬ ሳይሆን አይቀርም… የሆነ ሆኖ ከዚህ ቀጥሎ ጋሽ ስብሀት ፅፎት በሳቅ ፍርስ ካደረገኝ ጨዋታ መካከል የሚከተለውን እንድናወጋ ወደድኩ…  እንደሚከተለው አስታውሳለሁ!

በቀድሞ ግዜ ከነበሩ “ዋና ሰዎች” መካከል አሉ የሚባሉ አንድ ባለስልጠን ቀኛዝማች ይሁኑ ግራ አዝማች ወይም ፊታውራሪ ረስቼዋለሁ… ዘመቻ ሄደው ሲመጡ ታሪኩ ይጀምራል።

ዘመቻው ሁለት አመት የፈጀ ነበር። እናም ባለታሪካችን ከሁለት አመት ቆይታ በኋላ ነው  የሚመለሱት። መጀመሪያ የተቀበላቸው ታድያ ማነው…? ገብሬ። ገብሬ ማነው…? ገብሬማ የባለታሪካችን ዋና አገልጋይ ነው። ገብሬ እቃቸውን ተሸክሞ ከፊት ከፊት እየሄደ፤ መንገድ ላይ ጨዋታ ተጀመረ…

“እሺ ገብሬ ሀገሩ ሰላም ነው…?”

“ሰላም ነው ጌታዬ… ሁሉ ሰላም ነው… ብቻ…” አለ ገብሬ የጌታውን እቃ ተሸክሞ ከፊት ከፊት ኩስ ኩስ እያለ።

“ብቻ ምን…? አንተ የተፈጠረ ችግር አለ እንዴ?”

“የለም ጋሼ ብዙ አይደንግጡ… ብቻ መቻል መሞቱን ልነግርዎ ነው” አላቸው። መቻል ማነው…? ያላችሁ እንደሁ መቻልማ ባለታሪካችን አብዝተው የሚወዱት ውሻ ነበር።

“ውይ አፈር ስሆን… መቻል ሞተ…!?”

“አዎ ጌታዬ…! ሞተ…! ምፅ…” ኩስኩስታውን ገብሬ ቀጥሏል።

“ምን ሆኖ ሞተ በል…?” አሉ ባለታሪካችን፤ እንኳንም ሌላ መርዶ አልነገርከኝ በሚል ዜማ!

“አዬ… ጌታዬ ጉራች ታረደና የርሱን አጥንት ሲበላ ከጉሮሮው ላይ ስንቅር ብሎ አይሞቱ አሟሟት ሞተ…” ገብሬ በሱ ቤት ማሰተዛዘኑ ነው ለካስ ጉራች ደግሞ በጣም የሚወዱት በሬ ነበርና ጭራሽ ክው ብለው፤

“አንተ… ጉራች ለምን ታረደ በል…?” ብለው በቊጣ ጠየቁት።

“እሱማ… ለእሜቴ ተስካር  ነው ጌታዬ…!” አለ ገብሬ። እሜቴ እኮ ባለቤታቸው ናቸው!

ከቀደመው የእጥፍ እጥፍ ከዛም በላይ ሌላ እጥፍ ክውታ፤ ክው አሉ ባለታሪካችን! ጠላትዎ ክው ይበልና! ይሄኔ ገብሬም ኩስ ኩስ ማለቱን ትንሽ ገታ አደረገ።

“አንተ ምንድነው የምታወራው…? እሜቴ ሞተች ነው የምትለኝ…?”

“ምፅ… አዎ ጌታዬ እሜቴ ሞቱ እኮ!”

“የጉድ ሀገር…! ምን ሆና ሞተች መሆኑን?”

“አይ ጌታዬ… በወሊድ ነው!” (ልብ አድርጉልን ባለታሪካችን ከሁለት አመት በኋላ ወደ ቀያቸው መምጣታቸው ነው…)

“እንዴ… አንተ ሰውዬ ዛሬ ታመሃል እንዴ…? ከማን አረገዘችው…? እስቲ ንገረኝ…?” አሉ በቁጣ ተገስለው።

ይሄኔ ገብሬ ጣጣ አለው እንዴ…! ቀልጠፍ ብሎ መለሰ።

“እንጃ ጌታዬ ሰዉ ከገብሬ ነው ይላል እኔ ደግሞ ከኔ አይደለም እላለሁ!” ብሏቸው እርፍ።

በአግባቡ ተርኬው ይሆን? ብቻ ጋሽ ስብሀት ለመዘከር ያህል ነውና ልክ አንብው ሲጨርሱ “ጋሽ ስብሀት ነፍስህን ይማረው!” በማለት ተባበሩኝ! አመሰግናለሁ።

ማስታወሻ… ሽመልስ ሲሳይ የተባለ ወዳጃችን በነገረን ማብራሪያ መሰረት ጥቂት ማስተካከያ ተደርጓል ምስጋና ይገባዋል!

አንድ የምስራች፤ ሀገራችን ፈጣን እድገት አሳየች!

7ኛው ብሎግ በአስቸኳይ ደርሷል!

ትላንት ለሊቱን በሙሉ ማውጊያ ብሎጋችን ኢትዮጵያ ውስጥ የማይዘጋበትን መላ ሳንሰላስል ነበር። ታድያ አንዳች ዘዴ መጣልኝ። ልማታዊ ጨዋታዎችን  መጨዋወት ጥሩ ዘዴ እንደሚሆን አስብኩ። ታድያ ልማታዊ ዜና ከየት ይመጣል…? ብዬ ሳስብ፣ ሳስብ፣ ሳስብ… አንድ ወዳጃችን በዚህ ሳምንት ውስጥ በፌስ ቡክ ግድግዳው ላይ የለጠፈው አሪፍ ልማታዊ ዜና ትዝ አለኝ። ወዳጄ ስሙ ጠፋኝ… (ምን የስደተኛ ነገር እንኳን የሰው ስም የራሱንም ስም ይረሳል እኮ…! እናም ወዳጃችንን ይቅርታ ጠይቄ እቀጥላለሁ!)

ይህ ወዳጃችን የለጠፈው የምስራች ሮይተርስን ጠቅሶ ሲሆን፤ ሀገራችን አለ የተባለ እድገት እያሳየች እንደሆነ ያወሳል። ዕድገት ቢልዎት ደግሞ ዕድገት ብቻ አይምሰልዎ “ፈጣን እድገት” ብሎ ነው የዜና ወኪሉ ሮይተርስ የገለፀው። ታድያልዎ ክፉ ክፉውን ብቻ ሁሌ ከምናወራ እና ብሎጋችንንም ከምናዘጋ፣ ከፀሐዩ መንግስታችንም ከምንቀያየም ለምን እንዲህ ልማታዊ ጨዋታዎችን እየተጨዋወትን ግዜውን አንገፋም ስል አሰብኩ።

በርግጥ በሪፖርቱ ላይ የተገለፀው እድገታችን 7.5% የሚል ነው። በዚህ ብዙ ቅር አይበልዎ። ይሄ የምናዛሬ ጉዳይ ነው ድሮም ቢሆን ቁጥር በነርሱ ሲሆን ዝቅ በኛ ሲሆን ከፍ ይላል። እንኳንስ ሌላ ይቅርና ሰዓት ራሱ እኛ ሰባት ሰዓት ሆኗል ስንል እነርሱ አንድ ሰዓት ነው ይላሉ። ገንዘባቸውም እንደዛው ነው። እነሱ አንድ ሲሉ እኛ አስራ ሰባት እንላለን። ባጠቃላይ እኛ ቁጥር ላይ ቁጥ ቁጥ አናውቅም እነሱ ደግሞ የቁጥር ገብጋቦች ናቸው። ስለዚህ በእድገቱም 7.5 ቢሉንም 11.2% ጋር እኩል ነው እና ደስታዎን ይቀጥሉ።

አዎ መንግስታችንን ማመስገን አለብን! የእምነት ተቋማት ረዥም እድሜ ለምንግስታችን እንዲሰጠው ምዕመናኖቻቸውን ለፀሎት መጥራት አለባቸው። ባለውቃቢዎች የእድገት ባለቤት ያደረገን መንግስታችን ዘላለም እንዲኖር ውቃቢያቸውን መለማመን ይገባቸዋል። መጫኛ የሚያቆሙ ደብተራዎች መንግስታችንን እንደመጫኛው ቀጥ ብሎ እንዲቆም ጥበባቸውን ሊጠቀሙ ይገባል። (እዝች ጋ አሽሟጣጮች አሁንስ ተጠቅልሎ ነው ያለው? ብለው ፈታኝ ጥያቅ ቢጠይቁንም እንዳልሰማ እናልፋለን!)

የዚህ አይነት ዕድገት ባለቤት ያደረገን እርሱ ኢህአዴግ የተባረከ ነው! ብለንም እንዘምራለን! እልልታውንም እናቀልጠዋለን!

ሀገራችንን በአፍሪካ ፈጣን እድገት እያሳዩ ካሉ ሀገሮች ከቀዳሚዎቹ ተርታ አሰልፏታልና! እርስዎም ይደሰቱ! … እኔ በበኩሌ ደስታዬን ለመግለፅ ድግስ ሁሉ ለመደገስ አስቢያለሁ።    አስቡት እስቲ ከሃምሳ ምናምን አገሮች በእድገታችን ግንባር ቀደም ከሚባሉት ወገን መሆን ከየት ይገኛል? እውነቴን ነው የምልዎ እስከዛሬ ድረስ መንግስታችን ሲናገር ለፕሮፖጋንዳ ይመስለኝ ነበር። ለካስ እርሱቴ ምን በወጣው…! በእውነቱ ስናውቅ በድፍረት ሳናውቅ በስህተት ላንጓጠጥነው እና ላሽሟጠጥነው ይቅርታ መጠየቅ አለብን!

ወዳጃችን ከሮይተርስ ያገኘው ዜና ይህ ነው፤

Reuters- According to reports released by the International Monetary Fund, five of the fastest growing countries last 2011 are in Africa. This includes the countries of Ghana (13.5%), Eritrea (8.2%), Ethiopia (7.5%), and Mozambique (7.2%).

ምነው…? ምን ያስቅዎታል? አዎ ፈጣን እድገት እያሳዩ ያሉ ሀገሮች ውስጥ ተካተናል። በርግጥ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ኤርትራ በዕድገት ደረጃዋ ከእኛ ትበልጣለች። ይሁና! እባክዎ ወዳጄ አይሳቁ ብሎጉን እንዳያዘጉብን!

እኔም ሳቄ ሳያመልጠኝ ልሰናበትዎ… ካልተዘጋ በዚህ ከተዘጋ በሌላ ማውጊያ እንገናኛለን!